Fri. Sep 18th, 2020

የዐብዲ ኢሊ ተጎጂዎች ቅሬታ

ከዐስር ወራት በፊት፣ ሐምሌ 28፣2011 ዓ.ም.፣ በቀድሞው የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር ዐብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)፣ በክልሉ የመንግስት ባለስልጣናት እና “ሂጎ” በተሰኘው የወጣቶች ቡድን በጅግጅጋ ከተማ ንብረቶቻቸው ለወደሙባቸው ነጋዴዎች ከባለፈው ሳምንት አጋማሽ አንስቶ የማቋቋሚያ ክፍያ መክፈል ተጀምሯል፡፡

ከረጅም ውጣ ውረዶች በኋላ  በባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ግንቦት 14/2011ዓ.ም.፣ በባንክ አካውንታቸው የማቋቋሚያ ክፍያ የተፈጸመላቸው ነጋዴዎች፣ ከአዲሱ የክልሉ አስተዳደር ጋር ከተደረሰው ስምምነት ውጪ 25 በመቶ ቅናሽ ተደርጎ ክፍያ በመፈጸሙ ቅሬታ እንዳደረባቸው ለፍትህ መጽሄት ተናግረዋል፡፡


ከሐምሌ 28 ቀን ጀምሮ ለቀናት በቆየውና የጅግጅጋ ከተማን ባመሰቃቀለው ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከማለፉ ባሻገር፣ ብዛት ያላቸው አብያተክርስቲያናት መቃጠላቸው ፣ የብዙ ዜጎች እና ነጋዴዎች ቤት እና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡

የክልሉ አዲሱ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ወደስልጣን ሊመጡ የቻሉት፣ የሐምሌ 28 ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ፣ የፌዴራል መንግስት በቀጥታ ወደ ክልሉ ገብቶ የቀድሞው ርዕሰ-መስተዳድርን በቁጥጥር ስር ካዋላ በኋላ ነው፡፡

አቶ ሙስጠፋ ወደ ሥልጣን በመጡ በሦስተኛው ቀን የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎችን ለስብሰባ ጠርተው፣ በከተማው ላይ የተፈጸመውን ውድመት ዞረው በዐይናቸው ማየታቸውን እና በክልሉ ቀድሞ አስተዳደር አማካኝነት ለተፈጸመው ውድመት አስተዳደራቸው የካሳ ክፍያ ለመክፈል ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ሆኖም በሐምሌ 28ቱ ጥቃት የወደመው ንብረት ከፍተኛ በመሆኑ፣ በተጎጂ የከተማዋ ነዋሪዎች የቀረበውን የ700 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ የክልሉ መንግስት መክፈል እንደማይችል አሳውቆ ነበር፡፡

የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የካሳ ክፍያ ጥያቄው ከዐቅሜ በላይ ነው ካለ በኋላ ያቀረበው ሌላኛው አማራጭ፣ የ100 ሚሊዮን ብር ማቋቋሚያ ክፍያ መክፈል  ነው፡፡ ይህም በአነስተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ለሚገፉ የከተማው ነዋሪዎች የወደሙ ቤቶቻቸውን በፍጥነት እንዲያድሱ፣ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩትም በቶሎ ወደ ንግድ ሥራቸው እንዲገቡ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ትላልቅ ነጋዴዎች፣ በጥቂቱም ቢሆን፣ ከመቋቋሚያ ክፍያው ተካፋይ መሆናቸው ባይቀርም፣ ከወደመባቸው ከፍተኛ ሃብት አንጻር፣ ክፍያው አጥጋቢ እና ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፣ የክልሉ አስተዳደር ለእነዚህ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት ላደረጉ ነጋዴዎች፣ በክልሉ መንግስት ፕሮጀክቶች እና በብድር አቅርቦት በኩል ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶ ነበር፡፡

%d bloggers like this: