Sat. Oct 24th, 2020

የውጭ ጉዳይ ኦንላይን የውክልና አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ‘E-POA’ የተባለ ዲጂታል የውክልና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

አዲሱ የድጅታል ውክልና በውጭ የሚገኙ ዜጎች ከዚህ በፊት ኤምባሲ በመሄድና ውክልናቸውን በፖስታ በመላክ አገልግሎቱን ሲያገኙ የነበረበትን አሰራር ወደ ዘመናዊ መንገድ እንደሚቀይረው ነው የተገለጸው፡፡


ከ6 ወራት በፊት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የዲጅታል ኦንላይን አገልግሎት ደህንነቱ አስተማማኝ፣ ጊዜና ገንዘብን የሚቆጥብ ቀልጣፋ አሰራርን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንጽላ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ዮሐንስ እሸቱ ተናግረዋል፡፡

የኦንላይን ዲጂታል የውክልና አገልግሎቱ ዲያስፖራውን፣ ኤምባሲውን፣ ውጭ ጉዳይንና ተወካዩን የሚያገናኝ ሶፍትዌር በመጠቀም የሚሰራ ነው፡፡

በአሜሪካ በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን አገልግሎት ለማግኘት ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ባሉበት ቤታቸው ሆነው ፎርሙን ኦንላይ መሙላት በማስቻሉ የአገልግሎት ፍላጎቱ መጨመሩን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከኢምባሲው ጋር አብሮ ለመስራት ከተፈራረሙ ድርጅቶች ጋር በመሄድ ውሉን ፈርመው ክፍያ በመክፈል መረጃው ዋሽንግተን ዲሲ ወደሚገኘው ኢምባሲ በቀጥታ እንደሚተላለፍና ማረጋገጫ መስጠት የሚያስችል አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡

%d bloggers like this: