Fri. Sep 18th, 2020

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥነውን ፖለቲከኛና ፖለቲካ አላገኘም›› አቶ ሞላ ዘገዬ፣ የሕግ አማካሪና ጠበቃ

የሕግ አማካሪና ጠበቃው አቶ ሞላ ዘገየ፣ ሰኔ 24/2011ዓ.ም ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ-መጠይቅ

አቶ ሞላ ዘገዬ በይበልጥ በሕግ ባለሙያነታቸውና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን በማካፈልና በመሞገት ይታወቃሉ፡፡ ‹‹ውይይት›› በመባል በሚታወቀውና እሳቸው በሚያሳትሙት መጽሔት በርካታ መጣጥፎችን በአገራዊ ወቅታዊና መሰል ጉዳዮች ሲጽፉም ይታወቃሉ፡፡ ከሕግ ባለሙያነታቸው በተጨማሪ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ስለሚያስፈልጋት ለውጥና እንዴት መመራት እንዳለባት የሚያመላክት አነስተኛ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡


ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ከእርስ በርስ ግጭት ጀምሮ፣  የኢትዮጵያ መከራ ጊዜ የሚባሉት የትኞቹ ነበሩ? እነዚህን አስቸጋሪ ጊዜያት እንዴት መሻገር ተቻለ ብለው ያምናሉ?

አቶ ሞላ፡- ይኼ ሰፊ አርዕስት ነው፡፡ ረዥም ሰዓት ሊያናግር የሚችል ነጥብ ነው፡፡ ነገር ግን እጅግ በአጭሩ ለመናገር ያህል የቅርቡን ጊዜ ብጠቅስ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሕዝቡ በተለይም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በፊውዳሊዝም ሥር የነበረ ነው፡፡ ገባር ነበር፡፡ ጢሰኛ ነበር፡፡ ድርብ ድርድብ ጭቆና የነበረበት ነውና በዚያን ጊዜ ተማሪው መሬት ላራሹ ብሎ ተነሳ፡፡ ዝነኛ የሆነ መፈክር ነበር፡፡ ይህንን መፈክር አንግቦ ለዚያ አካባቢ ነፃነት ታግሏል፡፡ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለመሳሰሉት ጭምር ታግሏል፡፡ ነገር ግን ይኼ ስመ ገናና የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነበር፡፡ በዚህም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ምንም ዓይነት የዴሞክራሲ መዋቅር ያልነበረውና ሕዝብን አፍኖ ይገዛ ስለነበር፣ ለሰላማዊ ለውጥና ለሽግግር ቀዳዳ አልተወም፡፡ በዚህ የተነሳ አብዮት ፈነዳ፡፡ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ነው የተደረገው፡፡ ይኼ መሠረታዊ ለውጥ በርካታ ጥቅሞች አስገኝቷል፡፡ ለደሃውና ለሠራተኛው ጥቅም ይሆናሉ ተብለው የተወሰዱ ዕርምጃዎች ነበሩ፡፡ ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ካየኸው መሬት ለሕዝብና ለመንግሥት ሆኗል፡፡ ገበሬው ከፊውዳሊዝም ተላቋል፡፡ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ለከተማው ነዋሪዎች በሚጠቅምና በሚበጅ ሁኔታ ታውጇል፡፡ በተለይ የሃይማኖት እኩልነት በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ ሌሎችም መሠረታዊ የሚባሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ይህ የሆነው በሶሻሊዝም አይዲኦሎጂ በተመራ አብዮት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጥቅም ተገኘ?

አቶ ሞላ፡- ይህ በየትም አገር እንደተደረገው በዘመኑ አንድ ሦስተኛው የዓለም ሕዝብ ያለፈበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አብዮትም በዚህ መንገድ ነው ያለፈው፡፡ እርግጥ ነው የመደብ ትግል ነበር፡፡ የእርስ በርስ ግድያ ነበር፡፡ የሥልጣን ሽኩቻ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ ያቆጠቆጠና የበቀለ የብሔርተኝነት ጥያቄ ነበር፡፡ ይህ የብሔርተኝነት ጥያቄ ውሎ አድሮ በ1983 ዓ.ም. ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ ማዕከላዊ ሥልጣንን ለመያዝ ችሏል፡፡ ይህንን ሁሉ እንግዲህ ደምረህ ስትመለከተው አገሪቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ማለፏን ነው፡፡ ለዕድገት፣ ለግንባታና ለብልፅግና ሊውል ይችል የነበረው የአገሪቷ ሀብት ለእርስ በርስ ዕልቂት ውሏል፡፡ ይህ ኢትዮጵያን በጣም ይገልጻታል፡፡ ያንገበግባል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ነፃ አውጭ ነን የሚሉ ቡድኖች አዲስ አበባን ተቆጣጠሩ፡፡ የዚህኛውና የዚያኛው ብሔረሰብ ነፃ አውጭ ነን የሚሉ ቢሰባሰቡም፣ በፖለቲካ ረገድ ከደርግ የተሻለ  የፖለቲካ ሽግግር ያመጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ምንም ለውጥ ሳይመጣ ቀረ፡፡

ሪፖርተር፡- ደርግ ከወደቀ አዲስ አመራር መምጣቱ የፖለቲካ ለውጥ ወይም የፖለቲካ ትራንስፎርሜሽን ስለመደረጉ አያመለክትም?

አቶ ሞላ፡- የተደረገው የገዥ መለዋወጥ ነው፡፡ ኢሠፓ የሚባለው ገዥ ፓርቲ በኢሕአዴግ ተተካ፣ አይዲኦሎጂው ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግሥት፣ አውራ ፓርቲ እያሉ ያንቆለጳጵሱታል፡፡ በየጊዜው ስሙን ይቀያይሩታል፡፡ ነገር ግን የሌኒናዊ የፖለቲካ አደረጃጀት መርህን የተከተለ የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ እዚህ አገር የተተከለው ይኼ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ለ17 ዓመታት ከዚያ በኋላ ደግሞ ለ27 ዓመታት በጥቅል 44 ዓመታት ስንሰማ የነበረው ሶሻሊዝም፣ የነፃ ገበያ ካፒታሊዝም የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ወሬ ነው፡፡ ማለቴ እነዚህ አባባሎች ርዕዮተ ዓለማዊ መነባንብ ናቸው፡፡ እነ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት በቃላት ይነገራሉ፡፡ በተግባር የሉም፡፡ በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም እየተመራህ ሶሻሊስታዊ የፖለቲካ ሥርዓት አዋቅረህ በእሱ አገር እየመራህ፣ አንተ ግን ስለሊበራል ነገር ታወራለህ፡፡ የሕግ የበላይነትም ትላለህ፡፡ ነገር ግን በፍፁም ማርክሲስቶች ሥራ ላይ ሊያውሉት አይችሉም፡፡ በምንም ዓይነት ሌኒኒስቶችና ሶሻሊስቶች እነዚህን ሊተገብሩ አይችሉም፡፡ እነዚህ ሌኒኒስቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርገህ ነው የሕግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲና ነፃነትን የመሳሰሉ ትልቅ ሐሳቦች የሚያመጡት? ወሬ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከመጣ ጀምሮ ሲያወራ የነበረውን ትልልቅ ሐሳብ መተግበር አይችልም፡፡  

ሪፖርተር፡- የተመጣበት መንገድ እንዲህ ያለ ምሥል ካለው የአሁኑ ለውጥ ምን ዓይነት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አለው ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ሞላ፡- ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አንፃር በግልጽ ለመናገር ትራንስፎርሜሽን ያስፈልጋል፡፡ ይኼ እስካሁን የመጣንበት አደረጃጀት መቅረት አለበት፡፡ እስካሁን የመጣንበት መንገድ መቆም አለበት፡፡ ሪፎርሙ እኮ እሱ ነው መሆን የነበረበት፡፡ በእኔ እምነት ለውጡ መሆን የነበረበት ለ44 ዓመታት የመጣንበት ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ አደረጃጀትና ሥርዓት ነው፡፡ ያው ነው፡፡ ሌኒኒዝም ነው፡፡ አደረጃጀቱን፣ አወቃቀሩን፣ አመራሩንና አሠራሩን ካየኸው በኢሠፓና በኢሕአዴግ መካከል ልዩነት የለውም፡፡ ኢሠፓ ከሥር መሠረታዊ ድርጅት ጀምረህ እስከ ማዕከላዊ ሴክሬታሪያትና ፖሊት ቢሮ ድረስ የተዋቀረ ነው፡፡ ኢሕአዴግም እንዲሁ የተዋቀረ ነው፡፡ መንግሥቱን በቁጥጥር ሥር አውለውታል፡፡ ፓርቲውና መንግሥት ሚናቸው በቅጡ ካልተለየ በስተቀር፣ በምንም ዓይነት መንገድ ሪፎርም ወይም ትራንስፎርሜሸን የሚባል ነገር የለም፡፡ አሁን በተወሰነ ነገር ሪፎርም ተደርጓል፡፡ እኔ እንደተመለከትኩት በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ መሠረታዊ ሪፎርም ለማድረግና ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት ለመሸጋገር፣ አሁን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህ ሽግግር የሚቻልበት ሕግ ያለ በመሆኑ፣ ይህን በማስፈጸም ገበያውን ማረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ሞላ፡- ዋና ዋናዎቹን ልጥቀስ ካልኩ ለምሳሌ የፀጥታ ኃይሉ ፖሊስን ጨምሮ መጀመርያ ከፖለቲካ ነፃ መሆን አለበት፡፡ በየቦታው ቁልፍ ቦታ የተቀመጡት የፖሊስ መሪዎች በኢሕአዴግ አደረጃጀት አባል ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ አባል ካልሆንክ ሥልጣን አይሰጥህም፡፡ ይኼ ማለት እኮ አዲስ ፈሊጥ ልናመጣ አንችልም፡፡ ሌኒኒዝም እንዲህ ነው፡፡ በሌኒኒዝም የፓርቲ አባል ካልሆንክ ሥልጣን አይሰጥም፡፡ ሥልጣን ለማግኘትና ተጠቃሚ ለመሆን ነው የሚገቡት፡፡ ነገር ግን ይህንን ሲያደርጉ ሕዝብ እናገለግላለን እያሉ ነው፡፡ ሽፋኑ ሕዝብ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ መመራት የነበረበት በዚህ ነው፡፡ ሕግ አለ፡፡ መለየት አለብህ፡፡ በፖለቲካ ነው ወይስ በሕግ ነው የምትመራው? ዓላማው እኮ ይኼ ነው፡፡ አሁን ከላይ እስከ ታች የተዋቀረ ፓርቲ እኮ ነው የሚመራው፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ የሚወስነው ፓርቲው ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ ካድሬዎች ናቸው ይህንን የሚሠሩት፡፡ ስለዚህ ተቋማት በሕግ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን አሠራር ለመቀየር መልካም አጋሚ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ ይህ ምን ያህል ተሠርቶበታል? እየተሠራበትስ ነው?

አቶ ሞላ፡- አዎ ተጀምሯል፡፡ ሌላው እንደ ምሳሌ ላነሳው የምንችለው መጀመርያ ላይ ዶ/ር ዓብይ ከወሰዱዋቸው ጥሩ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የመከላከያና የደኅንነት መዋቅርን ከፖለቲካ ነፃ ለማድረግ ሙከራ መደረጉን ለማየት ችያለሁ፡፡ እኔ ይህንን በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ ለሥርዓቱ ቅርበት ስለሌለኝ በጥልቀት ምን እንደተሠራ አላውቅም፡፡ ደኅንነቱ በሕግ ይመራል፡፡ ደኅንነቱ የተቋቋመበት ሕግና አዋጅ አለ፡፡ በየደረጃው አለቃ አለው፡፡ ተጠሪነት አለው፡፡ ይህንን ተከትሎ መሥራት ነው፡፡ እዚህ ላይ ፓርቲ የሚባል ነገር አያስፈልግም፡፡ ሕግን ተከትሎ መሥራት ነው፡፡ የፓርቲው አለቃ ወይም በዚያ ውስጥ ያለው የኢሕአዴግ መዋቅር መጥቶ የጣቢያውን አዛዥ ጠርቶ፣ እገሌን እሰረው ሲለው አዛዡ አላስረውም ማለት አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው በሕግ ስለሚመራ ነው፡፡ ለማሰር በሕግ የሚደነግገው ሁኔታ ስላልተሟላ አላስርም ማለት ይችላል፡፡ እንዲህ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በሁሉም ተቋማት ውስጥ ሊኖር ይገባል፡፡ መንግሥት ከፓርቲው አሠራር መለየት አለበት፡፡ በሌላ አባባል እያልኩህ ያለሁት ኢሕአዴግ የሚባለው የፖለቲካ ድርጅት መፍረስ አለበት፡፡ ማቆም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- መፍረስ አለበት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ሞላ፡- ማቆም፡፡ በሕግ ማቆም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ምኑ ነው የሚቆመው?

አቶ ሞላ፡- ፓርቲውን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ማን ሊያደርገው ይችላል? ለምን? ሊሆንስ ይችላል?

አቶ ሞላ፡- ይህንን መንግሥት ያደርጋል፡፡ ፓርቲው ሊያደርገው ይችላል፡፡ ፓርቲው ራሱ ተሰብስቦ ይህንን ነገር ማድረግ አለበት፡፡ የፓርቲው ኮንግረስ ተሰብስቦ ፓርቲው ሪፎርም መደረግ አለበት፡፡ ሊብራል ዴሞክራቲክ መሆን አለበት፡፡ እንደዚህ ሪፎርም ከሆነ ደግሞ አደረጃጀቱ የተለየ ነው፡፡ የሶሻሊስት ፓርቲ አደረጃጀትና የዴሞክራቲክ ፓርቲ አደረጃጀት የተለየ ነው፡፡ አሠራራቸው የተለየ ነው፡፡ ይኼ ካልተደረገ በስተቀር አሁንም ችግሮች ይደጋገማሉ፡፡ ሌላ አገር እኮ ሪፎርም ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ምሥራቅ አውሮፓን ውሰድ፣ እዚያ የሶሻሊስት ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ የሶቭየት ኅብረት ኮሙዩኒስት ፓርቲ ነበር፡፡ ጎርባቾቭ ሪፎርም አደረገው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ሪፎርም በዚያ አልቆመም፡፡ ሁሉም በሶቭየት ኅብረት ጥላ ሥር የነበሩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች አሉ፡፡ ፓርቲዎቻቸው ሥራ ፈት ነው የሆኑት፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሆነበት ምክንያት ሲከተሉት የነበረው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተሻጋሪ ሊሆን አለመቻሉ ነው?

አቶ ሞላ፡- አዎ አይችልም፡፡ ሪፎርም ስትል መጀመርያ ሥራ የሚፈታው ፓርቲው ነው፡፡ ሥራ ፍለጋ ይሄዳል፡፡ ክፉ ነገር ይመጣባቸዋል እያልኩህ አይደለም፡፡ መዘጋት አለበት፡፡ በመንግሥት ሥራ ውስጥ መንግሥት በሕግ ብቻ መመራት አለበት፡፡ ይህንን ስናገር አንዳንድ ሰዎች ይቀባዥራል ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ግን እኔ እየቀባዥርኩ አይደለሁም፡፡ እኔ የማወራው ስለእውነተኛ ሪፎርም ነው፡፡ እውነተኛ ሪፎርም ከተባለ ሽግግሩ ከየት ወዴት ነው? ወንዝ ነው እንዴ የምንሻገረው? ሽግግሩ ከየት ወዴት ነው? ሽግግር የሚባለው ከሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ወይም በሶሻሊስት ርዕዮት ከሚመራ መንግሥታዊ አሠራር ወደ ዴሞክራሲያዊና ተቋማዊ አሠራርን ወደ መከተል ሥርዓት እንሸጋገር ማለታችን እኮ ነው፡፡ ሌላ ነገር የለውም፡፡ ይህንን ካላደረግን በስተቀር ሽግግር የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ አሁንም እኮ ያው ነው፡፡ የኢሕአዴግን ስም ትጠራለህ፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ሰው እኮ የጠላው ኢሕአዴግን ነው፡፡ አሠራሩን ነው የጠላው፡፡ ስሙን ነው የሚጠላው፡፡ ወይ ስሙ ይለወጥ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለሕገ መንግሥቱም ማንሳት ይቻላል፡፡ በሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ሞላ፡- ብሔር ብሔረሰብ የሚባሉ ተቋማት ናቸው ያሉት፡፡ ትልቁን ዕውቅና ያገኙት እነሱ ናቸው፡፡ ይኼ ማለት የሕገ መንግሥቱ ቀራጮች ነፃ አውጪዎች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ነፃ ለመውጣት የተደራጁ ናቸው፡፡ ነፃ እንውጣ የሚሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ነው፡፡ እንዲህ ብለው ነው የተደራጁት፡፡ እንዲህ ብለው ሲደራጁ ደግሞ ምን እያሉ መሰለህ? በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነገ ከነገ ወዲያ ሁኔታዎች አመቻችተው ይገነጠላል እያሉህ ነው፡፡ ካልተመቻቸው መብቶች ከተሸራረፉና የመሳሰሉ የሚለው ሰበብ ነው፡፡ ይገነጠላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን ነው የሚያወራው፡፡ መብትህ የተሸራረፈብህ እንደሆነ ለመገንጠል ጠይቅ ይልሃል፡፡ አንድ ላይ እንድንኖር አይደለም ሕገ መንግሥቱ የተቀመረልን፡፡ እንድንገነጣጠል ነው፡፡ እንድንለያይ ነው፡፡ ይህ ማንን ይጠቅማል ካልከኝ የሚጠቅማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ሌላው ይህ ሕገ መንግሥት በሚረቀቅበት ጊዜ ወይም ሐሳቡ በሚፈልቅበት ጊዜ የኢትዮጵያን እውነታ መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ፣ ይህንን ሕገ መንግሥት አረቀቅን የሚሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡት ሌላ ነው፡፡ ሌኒኒስቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ልትለወጥ የምትችልባቸው ብዙ መልካም ዕድሎች ነበሩ፡፡ እንደ መልካም ዕድል የታዩ ለውጦች ታይተው እንደነበር ይታመናል፡፡ ግን ሲበለሻሹ ይታያል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? አሁንስ?

አቶ ሞላ፡- መከራው ምን መሰለህ? በእያንዳንዱ መንግሥት ሥር ዴሞክራቲክ  ትራንስፎርሜሸን ሊያመጡ የሚችሉ ተቋማት እንዲፈጠሩ አይደረግም፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ምንም ዓይነት ተቋም አልነበረም፡፡ ከዚያም አብዮት ተካሄደ፡፡ የነበረውንም አፈራረሰው፡፡ በደርግ ጊዜ ምንም ዓይነት  ዴሞክራቲክ ተቋም የለም፡፡ ሕዝባዊ ንቅናቄና ሪፎርም እንዲደረግ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ተቋም የለም፡፡ የረቡ ፓርቲዎች የሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ብዙ ናቸው፡፡ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው? ምን ያህል ነው ይህንን ትልቅ ኃላፊነትና ይህንን ሕዝብ መርተው ወደ አንድ ደረጃ የሚያደርሱት? በግሌ በእነሱ ላይ አሁንም እምነት የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ብዙ ጊዜ አገሪቱ አግኝታቸው ነበር የሚባሉ መልካም አጋጣሚዎች መበላሸት፣ ከአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ካለመሆን ጋርም ይይዛሉ ማለት ይቻላል?

አቶ ሞላ፡- አዎ፡፡ ሌላው ሲቪል ማኅበረሰቡ ጠንካራ ያለመሆኑም እንደ ምክንያት ሊቀርብ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ሲቪል ማኅበራት ለመጠናከር ቢፈልጉ እንኳ ያልቻሉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡

አቶ ሞላ፡- አዎ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት መንግሥታቱ ናቸው፡፡ መንግሥታቱ ሆን ብለው እነዚህን የዴሞክራሲ መሠረተ ልማቶችን ያፈርሳሉ፡፡ እንዳይጠናሩ ያደርጓቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አገሩ ምድረ በዳ ነው፡፡ ምንም ነገር የለውም፡፡ ሁልጊዜ ይጮሃል፣ ለውጥ ይባላል፡፡ ለውጥ ይመጣል፣ እንዳልኩህ በ1966 ዓ.ም. ያልታሰበ ኃይል ነው ሥልጣኑን የወሰደው፡፡ ያልተጠበቀ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. የትም አይደርሱም ሽፍታ ናቸው ስንላቸው የነበሩት ወገኖች ሥልጣኑን ወሰዱት፡፡ አሁን ደግሞ ሪፎርሙ ካልታሰበ አቅጣጫ ነው የመጣው፡፡ ከኢሕአዴግ ውስጥ ሆኖ ካልታሰበ አቅጣጫ ነው የመጣው፡፡ እነ ዶ/ር ዓብይ፣ እነ አቶ ለማና ቡድናቸው ሥልጣን ይይዛሉ ብሎ ማንም የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ያልታሰበ ነው፡፡ በእርግጥ ፖለቲካ በፎርሙላ አይደለም፡፡ ፎርሙላ የለውም፡፡ 

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የለውጥ ሒደትስ?

አቶ ሞላ፡- ይህ ለውጥ ሲመጣ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለሪፎርም አልተዘጋጀም፡፡ ኅብረተሰቡም ለሪፎርሙ አልተዘጋጀም፡፡ ፓርቲዎች እንዲሁ ለሪፎርም አልተዘጋጁም፡፡ ይህንንም አላሰቡም፡፡ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ አሁን የምንተረማመሰው ለዚህ ነው፡፡ ምናልባትም መሪዎቹ በቅጡ አልተዘጋጁም፡፡ እነ ዶ/ር ዓብይም ቢሆኑ እኮ  የነበረውን ችግር ከማስወገድ ያለፈ፣ አስቀድመው ራዕይና ተልዕኮ ኖሯቸው ወደ ሪፎርም የመጡ ሰዎች ናቸው ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ ከሆነም እናያለን፡፡ የሚኖሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ በንግግራቸው የምንሰማቸው ነገሮች አሉ፡፡ በተናገሯቸው ንግግሮች ራዕይ አያለሁ፡፡ ራዕይ አላቸው፡፡ ትላልቅ ራዕዮችን ከንግግራቸው አያለሁ፡፡ ግን በትክክል ያንን ሊያስፈጽም የሚያስችል መዋቅር ተዘጋጅቶ የመጡ አልመሰለኝም፡፡ ገና እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን ገና ነን፡፡ አልተዘጋጀንም፡፡ ጅምሩ ጥሩ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን አልተዘጋጀንም፡፡ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ እኛ ሁልጊዜ የምናስበው አብዮት ነው፡፡ ያለው መንግሥት ይውደቅ ነው፡፡ ይኼ መንግሥት መባረር አለበት፣ መውረድ አለበት ነው፡፡ ሁልጊዜ የምንለው ይህንን ነው፡፡ በምን እንተካዋለን የሚለውን ግን አስበን አናውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዳሉት ለየት ያለ ነገር ይዘው መጥተዋል፡፡ በዚሁ ምክንያት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡ እየቆየ ግን በአንዳንድ ወገኖች የተደበላለቁ ስሜቶች ይታያሉ፡፡ ይህ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ሞላ፡- ቀዝቀዝ አለ፡፡ ግስጋሴውም ቀዝቀዝ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ሞላ፡- ለምሳሌ ዶ/ር አብይ ከመጀመርያው ጀምሮ የሄዱበት መንገድ በጣም ነው የምደግፈው፡፡ ለምሳሌ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እስረኞችን መፍታታቸው በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ምሕረት ማበጀታቸው በጣም ጥሩና ድጋፍ ያሰጣቸው ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ የምሕረት ዕወጃ ግን በከፊል ነው፡፡ እዚህ ላይ ተዓቅቦ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ተዓቅቦዎ ምንድነው? በከፊል የተሰጠ ምሕረት የሚያሰኘውስ?

አቶ ሞላ፡- ምሕረቱ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል አገለገለ፡፡

ሪፖርተር፡- የትኛውን?

አቶ ሞላ፡- የቀድሞ መንግሥት አባላትን፡፡ ይኼ ተደናግጦ የነበረውና በሪፎርሙ ምክንያት ግራ ገብቶት የነበረው የሆነ የፖለቲካ ልሂቅ ሰብሰብ ብሎ፣ አጠቃላይ ምሕረት  ደርግን መጨመር የለበትም የሚል ኃይል ተነሳ፡፡ እስኪ ተመልከት እንግዲህ ዶ/ር ዓብይ ምሕረቱን ሲያውጁ ይህንን አላሰቡም፡፡ በውስጣቸው መልካም ነገር ነው ያሰቡት፡፡ ይህንን ያደረጉት ቅሬታ እንዲቆም ነው፡፡ ደርግ ለብቻው ተገልሎ ስለአምስት ሚሊዮን ሕዝብ እኮ ነው የምናወራው፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም አባላት አምስት ሚሊዮን ናቸው፡፡ ባለፈው ጊዜ ቀይ ሽብር ተብሎ፣ ዘር ማጥፋት ተብሎ የሌለና ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተፈጸመ እንደተፈጸመ ተደርጎ ተደነገገ፡፡ በዚያን ጊዜ ዘር ማጥፋት አልተፈጸመም፡፡ የተፈጸመው የፖለቲካ ግድያ ነው፡፡ የእርስ በርስ ግድያ ነው፡፡ የሲቪል ጦርነት ነው፡፡ ዘር ማጥፋት አይደለም፡፡ የጦር ወንጀል የለም፡፡ ይኼ በሌለበት ሁኔታ ያንን የኅብረተሰብ ክፍል ለማንቃት የፈለጉ ወገኖች ይህንን ድርጊት ዘር ማጥፋት እንበለው አሉ፡፡ አሉት፡፡ የሕግ ሽፋን ሰጡት፡፡ ፍርድ ቤትን አዘው አስባሉት፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አሁን ደግሞ አጠቃላይ ምሕረት ሲባል እነዚያው ሰዎች በዘር ማጥፋት የተከሰሱ ሰዎች ምሕረቱ አይገባቸውም አሉ፡፡ ምክንያቱም ይኼ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተጠቅሷል ይላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጠቀሰ ይህንን እንዴ ማስተካከል ይቻላል? ዶ/ር ዓብይ ለብቻቸው የሚለውጡት አይደለም፡፡

አቶ ሞላ፡- እንዴ. . . የሌለ እኮ ነው፡፡ የለም፡፡ እኔ ጮኼ ጮኼ ሰው ያልሰማኝ ይኼንን ነው፡፡ እንደ ትልቅ አጀንዳ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ስንት ሺሕ ሕዝብ ነው በዚህ ምክንያት የተሰደደው? የባህር ኃይል አባላት፣ የአየር ኃይል አባላት፣ የምድር ጦር አባላት፣ ሌላውም ባለሙያ በሙሉ፣ አገሪቱ ስንት ሀብት ያፈሰሰችበት የፀጥታ ኃይል፣ በተለይ ፓይለቶች ሳይቀሩ አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ሌላ አገር እያገለገሉ ነው፡፡ ለምንድነው ይህ የሚሆነው? የእኔ ጥያቄ ይህ ምሕረት ተጀምሮ የሆነ ቦታ ተጨናገፈ ነው፡፡ ጮህን ሰሚ የለም፡፡ ይህ መታረም ነበረበት፡፡ አሁንም መታረም አለበት፡፡ አምስት ሚሊዮን ብዙ ነው፡፡ ይኼ ኅብረሰብ አኮረፈ፡፡ በፖለቲካው ድምፁን አያሰማም፡፡ አልተደራጀም፡፡ በየአገሩ ተሰዶ ነው ያለው፡፡ አንገቱን ደፍቶ ነው ያለው፡፡ በፖለቲካ ተሳታፊ እንዳይሆን፣ በአገሩ ጉዳይ ድምፅ እንዳይኖረው ተከለከለ፡፡ በሌሎች የሞት ፍርድ ለተፈረደባቸው ሰዎች ምሕረት ካደረግክ፣ ለእነዚህ ለምን ትነፍጋለህ? ለምሳሌ ጣሊያን ኤምባሲ ያረጁ ሽማግሌ ሰዎች እንኳን በዚህ ምክንያት እንዳይፈቱ ተደርጓል፡፡ ሕመምተኞች ናቸው እነሱ፡፡ ምን ማለት ነው? ስለዚህ አንዱ እንቅፋት ይኼ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ስሜትን ቀዝቀዝ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ አሁንም መታረም አለበት፡፡ ዶ/ር ዓብይ መጀመርያ ልባቸው የሚነግራቸውን ነበር የሚያደርጉት፡፡ በእኔ እምነት ልባቸው የሚነግራቸው ልክ ነበር፡፡ መሪ ህሊናውና ልቡ የሚነግረውን ሲያደርግ ነው ስኬታማ የሚሆነው፡፡ መሪ በጭንቅላቱ ማሰብ ከጀመረ መወሰን አይችልም፡፡ በጭንቅላት ማሰብ የአማካሪዎችህ የኤክስፐርቶች ሥራ ነው፡፡ መሪ ከነበርክበት ወዳልነበርክበት የሚወስድህ ነው፡፡ መሪ ማለት ይኼ ነው፡፡

ያልነበርክበት ላይመችህ ይችላል፡፡ ሕዝቡ የነበረበትን ሊወድ ይችላል፡፡ ባለ ራዕይ መሪ ግን ከዚያ ውስጥ ፈንቅሎ ነው የሚያወጣህ፡፡ ዓብይ ግን ወዳልነበርንበት ወሰዱን፡፡

ሪፖርተር፡- ግልጽ ያድርጉልኝ፡፡ ወዴት?

አቶ ሞላ፡- ፍቅር፣ ሰላም፣ መተሳሰብና ይቅርታን ሳናስበው አመጡልን፡፡ ቃላቱን አመናቸው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ልክ ናቸው አልን፡፡ አልተነጋገርንም፡፡ ስለምሕረት ማን ተነጋገረ? ወያኔ/ኢሕአዴግን ስለመማር ማን ተናገረ? ሕዝቡ ተሰብስቦ መቼ መከረ? መቼ ተነጋገረ? በቃ ዶ/ር ዓብይ ብለዋል ብለን ከእኔ ጀምሮ ሁላችንም ተቀበልን፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ምን ያሳያል?

አቶ ሞላ፡- ዶ/ር ዓብይ እስከዚያ ሰዓት ድረስ ለእኔ ልባቸውን ነበር የሚከተሉት፡፡  ልባቸው የሚመራቸውን ነበር የሚከተሉት፡፡ አሁን አማካሪ በዛና ወደ አዕምሯቸው የተመለሱ ይመስለኛል፡፡ ገደል ገደሉን ለመምራት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ አንድ እንቅፋት ተፈጠረ፡፡ ቀጥሎ እስረኛ መፍታት፣ አጠቃላይ ምሕረት በማወጅ ሪፎርም እያካሄድክ አይደል? ቀጥሎ መደረግ ያለበት ብሔራዊ ንግግር ነበር መጥራት ነው፡፡ ፓርቲ አይደለም መጥራት ያለብህ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም መጥራት ያለብህ፡፡ እነሱ ማንን ይወክላሉ? ምን ማኅበራዊ መሠረት አላቸው? ምን መሠረት አላቸው? የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል አይወክሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ደጋፊና የሚወክሉት የኅብረተሰብ ክፍል ይኖራቸዋል፡፡ በአገሪቱ ጉዳይ  ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጠርቶ ማነጋገር ተገቢ አይደለም?

አቶ ሞላ፡- አዎ፡፡ እነሱ እንወክላለን ይላሉ፡፡ ግን የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ይወክሉኛል ብሎ ተናግሮ ያውቃል? ስለዚህ በእኛ በኩል ብዙ ችግር አለ፡፡ ቀደም ብለህ እንደጠየቅከኝ በተደጋጋሚ መልካም ዕድል የሚያከሽፉት ዋነኛ ምክንያቶች ብዬ የምጠቅሰው፣ ሁልጊዜ የምናመጣቸው ሐሳቦች የተውሶ ስለሆኑ ነው፡፡ አገር በቀል አይደሉም፡፡ ከትምህርቱ ጀምሮ የሠለጠነ ሰው የምትለው ሁሉ የሥልጣኔ መሠረቱ አገራዊ አይደለም፡፡ እንደገና በፖለቲካውም በ1966 ዓ.ም. ከምሥራቅ ሌኒኒዝምን ተዋስን፡፡ ማኦኒዝምንና ማርክሲዝንም አምጥተን እዚህ አገር ሥራ ላይ አዋልን፡፡ በፍፁም ሥራ ላይ መዋል ያልነበረበት ነው፡፡ ይዋልም ከተባለ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ነበር መዋል የነበረበት፡፡ ስለዚህ ወደ ውስጥ የመመልከት ችግር ነው፡፡ የተቋማት አለመኖርም ሌላው ችግር ነው፡፡ በተለይ የምንዋሰው የፖለቲካ አስተሳሰብ ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ያለመጣጣሙ ነው፡፡ ለምሳሌ ሌኒኒዝምን አመጣን፡፡ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አይጣጣምም፡፡ ኅብረተሰቡ አያውቀውም፡፡ ስለማናውቀው ኅብረተሰብ ነው የምናወራው፡፡ አሁን 100 ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኅብረተሰቡ ውስጥ አብሮ የኖረ፣ ኅብረተሰቡን በተለያየ ደረጃ ያገለገለ፣ ችግሩን ያወቀ ምን ያህሉ ነው? አገሪቱን የሚያውቀው ምን ያህሉ ነው? የሁሉንም የአገሪቱ ዜጎች ጉዳይ ማወቅ አለብህ፡፡ የሶማሌውን ባህል ማወቅ አለብህ፡፡ የአፋሩ፣ የቤንሻንጉል ጉምዙን ማኅበራዊ ችግሩ ምንድነው? እንዴት ነው የሚፈታው? ብለህ ልታውቅ ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ነው የጠሩት፡፡ እኔ ድፍረት ካልሆነብኝ ችኮላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠርቶ ማነጋገሩ ምኑ ነው ችኮላ?

አቶ ሞላ፡- ችኮላ ነው ያልኩት፡፡ ስህተት ነው አልልም፡፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያትዎ ምንድነው?

አቶ ሞላ፡- በእኛ አገር አደረጃጀት፣ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ኅብረተሰቡን የሚወክሉት የአገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ አብረውት ነው የሚኖሩት፡፡ በገጠር ደግሞ ሽበት ስላለህ ሽማግሌ አትባልም፣ ይታወቃል፡፡ የእከሌ ዝርያ ተብለህ በዚያች ትንሽ ማኅበረሰብ ውስጥ የምትታወቅ ሰው ነህ፡፡ ስለዚህ ፍርድህ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ናቸው የአገር ሽማግሌዎች፡፡ እነዚህ ስለሚኖሩበት አካባቢ እውነታውን ይነግሩሃል፡፡ አንተ እዚህ የምትለፈልፈው ችግርና እነሱ መሀል ያለ ችግር የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ መሆኑን የዚያን ጊዜ ታየዋለህ፡፡ ሌላው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው፡፡ የሞራል ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ዛሬም እኮ የሚያስተዳድሩት እነሱ ናቸው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ዛሬ እየበጠበጠ ያለው ካድሬው ነው፡፡ ሌላ ነገር እንዳይመስልህ፡፡ ይህንን ሕዝብ የሚያስተዳደረው የኢትዮጵያ ሕግ እዚያ ድረስ ወርዶ አይደለም፡፡ ገጠር ስትሄድ የእኛ ሕግና የእናንተ ሕግ ነው የሚሉት፡፡ የእነሱ የመተዳደሪያ ሕግ አለ፣ ባህል አለ፡፡ ሽምግልና የራሱ ሰዓት አለው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች የሕዝቡን ብሶት በአደባባይ ይናገራሉ፡፡ ሁሉም ዘንድ ሄደው ይናገራሉ፡፡ ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች አሉ፡፡ አሁን ከምትለው የበለጠ የዚያን አካባቢ ምን እንደሚፈልግ ይነግሩሃል፡፡ እነሱ ነበር መምጣት የነበረባቸው፡፡ አሁንም እነሱ ናቸው መምጣት ያለባቸው፡፡ ሌላው ፓርቲ የት ያውቀዋል?

ሪፖርተር፡- እርግጥ እነዚህን እሴቶች በአግባቡ መጠቀም ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በአንፃሩ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የመሳሰሉትን በመጠቀም መጓዝ ቢቻል አሁን እየታየ ያለው ወጣ ያለ ነገር ለምን ተፈጠረ ይላሉ? እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም? ችግሩ ምንድነው? ሽማግሌዎች አልተደመጡም?

አቶ ሞላ፡- እነሱ መቼ ዕድል አገኙ? ማን ያናግራቸዋል? አሁንም እኮ ችግራችንን የሚፈቱት እነሱ ናቸው፡፡ የሽማግሌን ችግር ማነው የሚፈታው? የአገር ሽማግሌ ነው፡፡ እኔ ከመሬት ተነስቼ አይደለም የማወራልህ፡፡ እኔ ከዓመታት በፊት የጅግጅጋ አስተዳዳሪ ነበርኩ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ [የኢትዮጵያና የሶማሊያ] አስተዳዳሪ ነበርኩ፡፡ ከዚያ የተማርኩት ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ ለምሳሌ ከጅግጅጋ አስከ ደገሃቡር ድረስ ያለው መንገድ በፈንጂ የታጠረ ነበር፡፡ ለዚያ ወታደር አላሰማራሁም፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን ነው የጠራሁት፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች (ኡጋዞች) ጅግጅጋ ውስጥ አሉ፡፡ እነሱን ጠርቼ ይህንን ችግር እንዴት እንፍታው ነው ያልኳቸው፡፡ ከዚያ እያንዳንዱ የጎሳ መሪ ከጅግጅጋ እስከ ደገሃቡር ድረስ ጎሳውን አዘዘ፡፡ ንቀል አለው፡፡ ፈንጂውን አወጡት፡፡ እኔ የፈንጂ መርማሪ ነው ከሠራዊቱ የመደብኩላቸው፡፡ አንድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ሽማግሌዎችን ነው የምጠራው፡፡ ካድሬ አይደለም የምጠራው፡፡ ስለዚህ አሁንም ግልብ አስተሳሰብን ወደ ጎን ትተን የምንሠራው ለሕዝቡ ከሆነ ሕዝቡን ለምን እንንቃለን? ሕዝቡ ውስጥ ጥበብ አለ፡፡ ከቁብ አልቆጥር አልነው እንጂ ሕዝቡ ዘንድ ብዙ ነገር አለ፡፡ እኛ በሕዝብ ስም እንነግዳለን፡፡ በእሱ ስም እንነግዳለን፡፡ እሱን ግን እንሰማውም፡፡ ለምን? እስከ ዛሬ በተውሶ ከጻፍነው ሕግ የተሻለ ሕግ አለው፡፡ ሁሉም ሕዝብ አለው፡፡ ይህንን ትተን ነው የምናንጋጥጠው፡፡ ይህንን እውነት የሚቀበል የፖለቲካ ልሂቅ እስኪፈጠር ድረስ ይኼ ችግር ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ሽማግሌዎችና በኅብረተሰቡ ነባር እሴቶች አለመጠቀም ወደፊትም ችግር ሊሆን ይችላል ካሉ፣ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ምንድነው? ይህንንም መፍትሔ ለመተግበር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ሞላ፡- አገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው መቀረፅ  ያለበት፡፡ ስለዚህ እኔ የምለው አሁንም ቢሆን ስለአወካከሉ ምን ያህል ሰው ይሰብሰብ፣ የት ይሰብሰብና አጀንዳ ምን ይሁን የሚል ዝርዝር ነው፡፡ ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ የኢትዮጵያን ራዕይና ተልዕኮ የሚቀርፀው አሁን የማወራልህ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ሕዝቡ ነው፡፡ ይኼ ነው መምጣት ያለበት፡፡ ሕዝብ ባዶ ቃል አይደለም፡፡ በማን እንደሚወከል ነግሬሃለሁ፡፡ ቢያንስ የተሻለ ነው፡፡ ፍፁም ነው ባልልም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ይልቅ የሃይማኖት አባቶች ይወክሉታል፡፡ በተሻለ የአገር ሽማግሌዎች ይወክሉታል፡፡ በተሻለ ታዋቂ ሰዎች ይወክሉታል፡፡ ይኼንን ሪፎርም እየመራ ያለው ኃይል መነጋገር ያለበት ከእነዚህ ጋር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ራዕይ ከዚያ ውስጥ ይፈልቃል፡፡ አሁን እንደምናየው ነፃ አውጪ ነን የሚሉት እንደሚሉን አይደለንም፡፡ የፖለቲካ ልሂቁ የሚፈራው ይህንን ነው፡፡ መንግሥት የዜጎቹን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር አለበት፡፡ በወታደር አትዘልቅም፡፡ ሕዝቡ ዘንድ መውረድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አገር የሚያምሰው የሌኒኒዝም ካድሬ ነው፡፡ ለሥልጣን የሚታገለው እሱ ነው፡፡ ሕዝቡ ወሳኝ ሚና መጫወት እየቻለ ተመልካች ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ እነዚህ የጠቀስኩልህ ሕዝብን ይወክላሉ ያልኩህ አካላት አማካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን አትንኩት ይባላል፡፡ ሕዝቡ መቼ ነፃ ልውጣ አለ? ኢትዮጵያ የምትባለው ዓለም የሚያውቃት ነች፡፡ በዚህ በኢትዮጵያ ግዛት ከተወለድክ ኢትዮጵያዊ ነህ፡፡ አንተ ባትፈልገውም ኢትዮጵያዊ ነህ፡፡ አለቀ፡፡ እንዴት ነው ከዚህ ነፃ ልውጣ የምትለው? የአስተዳደር በደል ደርሶብሃል? አዎ! ሁሉም ነው የደረሰበት፡፡ የሥርዓቱ በደል አለ፡፡ የተጠቀመም አለ፡፡ የተበደለም አለ፡፡ ሁሉም 27 ዓመታት ሲገዛ በደል ደርሶበታል፡፡ ጥያቄው እኮ በደሉን እናስቀር ነው፡፡ ግን ብልጦች ሊያታልሉት ይፈልጋሉ፡፡ ነውር ነው፡፡ እንዴት ነው ይህንን ሕዝብ የሚንቁት? ስለኢትዮጵ ሕዝብ ደሃ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዶ/ር ዓብይ ከሚናገሩት በላይ መናገር አልችልም፡፡ እሳቸው የሚሉትን በሙሉ እቀበላለሁ፡፡ ትልቅ ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥነውን ፖለቲከኛና ፖለቲካ አላገኘም፡፡ እንዲያውም ሁሉንም ነገር አጥርቶ ለማግኘት ከሕዝብ ቆጠራው ጎን ለጎን እንዴት መተዳደር ትፈልጋህ ብለህ ብትጠይቀው መልሱን ታገኛለህ፡፡ ይህ መደረግ አለበት፡፡ ስለሕገ መንግሥትም ቢሆን ይጠየቅ፡፡ ያኔም መልሱን ታገኛለህ፡፡ ልሂቃን አይደሉም መወሰን ያለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ያለ ሕገ መንግሥት ነው የምፈልገው ብሎ ቢቀርብ፣ ዶ/ር ዓብይ የሚቀበሉ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ነው አሁን ቀዝቀዝ ስላለ ነው እዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ የገባነው፡፡ ሪፎርሙ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ ከዚያ መውጫ አላበጁም፡፡ ዶ/ር ዓብይን አስፈሯቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከላከል አሉ፡፡ ሕግ እኮ የምትፈጥረው አንተ ነህ፡፡ እሳቸው በቅን ልቦና እየሄዱ እያሉ አቆሟቸው፡፡ አማካሪው በዛ መስማት የለባቸውም፡፡ አይስሙ ስልህ በተለይ አንዳንድ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በራሳቸው፣ የመሪ ፈተና በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻቸውን ይወስኑ፡፡ መወሰንም ይችላሉ፡፡ ኃላፊነቱን የሚወስዱት እሳቸው ናቸው፡፡ ሕዝብ ይደግፋቸዋል፡፡ ይህንን ቀናነት ይዘው በልባቸው በሚወስኑት ውሳኔ ቢያጠፉ፣ ወይም በዚያ ውሳኔ ባንስማማ እንኳን ግድ የለም ልንል እንችላለን፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ሲሰበሰቡና ካድሬዎች ሲሰበሰቡ የሚነግሯቸው ነገር የተለያየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጉዳዮች ቅራኔዎች ይታያሉ፡፡ ግጭቶችም እየታዩ ነው፡፡ በበለጠ ደግሞ ከሰሞኑ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ እጅግ አሳዛኝ ግድያዎች ታይተዋል፡፡ ግድያዎቹ የታወቁና በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ አንቱ የሚባሉ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት አሳጥቷል፡፡ ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ሞላ፡- ሰሞኑን ስለተፈጠረው ሁኔታ አስተያየት ለመስጠት መረጃ ይጎለኛል፡፡ ብዙ ነገር የለኝም፡፡ የተደረገው ድርጊት ግን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ መራር ነው፡፡ ያዘንኩት ግን እኔ የማያምሩኝ ነገሮች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- የማያምሩኝ ነገሮች ነበሩ ሲሉ?

አቶ ሞላ፡- እኔ ወታደር ነኝ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ በአስተዳደርም፣ በፀጥታም በኩል ውስን ልምድ አለኝ፡፡ እኔ ይኼ በየክልሉ የፀጥታና የሚሊሻ ሠራዊት እየተባለ የሚደራጀው ነገር ፈጽሞ አያምረኝም፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ምክንያትዎን ይንገሩኝ፡፡ ይህንን ያሉት ከምን በመነሳት ነው?

አቶ ሞላ፡- ከመጀመርያው ጀምሮ አያምረኝም ያልኩት፣ ሲጀመር በክልል ማደራጀቱ ለምን እንደተፈለገ ግራ ስለሚያጋባ ነው፡፡ አንተ ማጠናከር ያለብህ ፖሊስ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እነዚህን የመሳሰሉትን ማጠንከር ነው፡፡ ነገር ግን በየክልሉ የሚሊሻ ጦር፣ የፀጥታ ኃይል እየተባለ የሚጠራው የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ነው ሲባል እሰማለሁ፡፡ አይደለም፡፡ በጦር የሕግ የበላይነት አይከበርም፡፡ የሕግ የበላይነት የሚከበረው በሕግ ነው፡፡ ሕግን ደግሞ በግንባር ቀደምትነት የሚያስከብረው ፖሊስ ነው፡፡ በክልል ፕሮፌሽናል ፖሊስ ለማደራጀት ገንዘብ ብታወጣ ይስማማኛል፡፡ ፕሮፌሽናል ፖሊስ ብታደራጅ ልክ ነው እላለሁ፡፡ ነገር ግን ሚሊሻና ልዩ ኃይል እያልክ የምታደራጅ ከሆነ የተለየ ዓላማ አለህ ብዬ ነው የምጠረጥርው፡፡

ሪፖርተር፡- ያብራሩልኝ? በክልሉ የልዩና የፀጥታ ኃይል መደራጀት የተለየ ዓላማ ምንድነው?

አቶ ሞላ፡- አዎ በክልል ጦር ስታደራጅ የተለየ ዓላማ አለህ ብዬ ነው የምጠረጥርህ፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂው ከሌላ ክልል ጋር የተያያዘ ነገር አለው፡፡ የትግራይ ክልል ሚሊሻ ይሉሃል፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ሚሊሻ ይሉሃል፡፡ የሶማሌ ክልል ሚሊሻ ይሉሃል፡፡ ይኼ ምን ማለት ነው? አይሆንም፡፡ ስለዚህ አንድ ለምትፈልገው ዓላማ  ይህንን ኃይል አደራጅተህ ለመጠበቅ ነው ፍላጎቱ፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል አስተዳደር ባላቸው አገሮች እንዲህ ያለው አደረጃጀት ቢኖርስ?

አቶ ሞላ፡- ስለፌዴራሊዝም እኛ አገር መነጋገር አለብን፡፡ ይኼ ሌላ አጀንዳ ነው፡፡ ነገር ግን የእኛ አገር ዴሞክራቲክ ፌዴራሊዝም አይደለም፡፡ የሶሻሊስት ፌዴራሊዝም ነው፡፡ የሶቭየት ኅብረት ዓይነት ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ፓርቲው የሚቆጣጠረው አስተዳደር ነው፡፡ ይኼ ፌዴራሊዝም አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ የሚቆጣጠረው ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ይኼ የተቀረፀበትና የተፀነሰበት የመጨረሻው ዓላማ አለው፡፡ ቢሳካ ለመገንጠል ነው፡፡ ግን አይሳካም፡፡ የኢትዮጵያን እውነታ የማንፀባረቅ አስተሳሰብ ስላልሆነ ይከሽፋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ በየክልሉ ያሉ ሚሊሻ የሚባሉት ለእኔ ጉልበተኞች ናቸው፡፡ ጉልበት ነው የምትገነባው፣ ኃይል ነው የምትገነባው፣ መሆን የሌለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ የራሷ ዓርማ አላት፡፡ ፕሮፌሸናል ሠራዊት አላት፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ከፖለቲካ አመራሩ ተፅዕኖ ነፃ የወጣ የሚመስል ፕሮፌሽናል ሠራዊት አላት፡፡ ዝርዝሩን አላውቅም፡፡ በካድሬ እየታዘዘ እገሌን እሰር፣ እገሌን ስልኩን ጥለፍ፣ እገሌን ተከታተለው፣ የማይባል ፕሮፌሽናል የደኅንነት ዘርፍ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ባለበት ጊዜ፣ እንደገና በገጠር ጦር የምታደራጅ ከሆነ ዝርዝሩ ባይኖረኝም መጨረሻው ሰሞኑን የሆነውን ዓይነት ነው የሚከሰተው፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላውቅም የሆነው ይኼው ነው፡፡ አንድ የማውቀው ነገር አለ፡፡ ሚና ተለይቶ ተተኮሰ፡፡ የማይተኩ ሰዎች ሞቱ፡፡ ይኼ ድርጊት ሊፈጸም አይገባም ነበር፡፡ ባህር ዳር ላይ የተደረገው ከአዲስ አበባው ግድያ ጋር ይያያዝ አይያያዝ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- መገዳደል ግን ለዚህ ዘመን ይመጥናል?

አቶ ሞላ፡- ይኼ ቆሻሻ ነገር ነው፡፡ መጥፎ ባህል ነው፡፡ ቆሻሻ ባህል ነው፡፡ መጥፎ ባህል ነው፡፡ ፖለቲካውን ወደ ባለቤቱ እንመልሰው፡፡ ፖለቲካው አስመሳይ ልሂቃን እጅ ውስጥ ስለሆነ እኮ ነው፡፡ ሕዝብ የሕገ መንግሥት ሐሳቦችን ያፍልቅ፡፡ በተወካዮቹ አማካይነት አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ይነጋገር፡፡ ሪፎርሙ እንዴት መቀጠል እንዳለበት ይወስን፡፡ ይህንን ነገር ዶ/ር ዓብይ ያስፈጽሙ፡፡

ሪፖርተር፡- የሰሞኑ ግድያ ፍራቻን ፈጥሯል፡፡ ከሐዘኑ በላይ ቀጣዩ ጉዞስ የሚል ጥያቄ ያስነሳልና እንደገና እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት? ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥትና ሌሎች አካላት ምን ሊያደርጉ ይገባል? እንደ እናንተ ያሉ ሰዎችስ?

አቶ ሞላ፡- እኛማ ይህንኑ ሐሳባችንን ማጋራት ነው፡፡ በግሌ ችግሮን አንስቼ መፍትሔውንም እጠቁማሁ፡፡ በራሴም ሚዲያ እናገራለሁ፡፡ ሌላውም እንዲሁ ማድረግ አለበት መጮህ አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ በቀላሉ የምተው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ስለኢትዮጵያ ምን ይታይዎታል?

አቶ ሞላ፡-አሁንም አንድ መንገድ ነው ያለን ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሌሎች አሥር መንገዶች ሊኖሯቸው ይችላሉ፡፡ እኔ የሚታየኝ ብሔራዊ ንግግር ነው፡፡ አሁን አንተ ባነሳሃቸው ጥያቄዎች ላይ ሕዝቡ መነጋገር አለበት፡፡ ሕዝብ ያውቃል፡፡ ከባህሉና ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ ምን መደረግ እንዳለበት ያውቃል፡፡ የሕዝቡን ችግር እንወቀው፡፡ እውነት አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ አገር ተገንጥሎ መንግሥት አቋቁሞ፣ ከሌላው በችግር ከተሳሰረው ወገኑ ተለይቶ መኖር ይፈልጋል? አይደለም፡፡ ከውጭ መጥተው ይህንን እያሉ ነው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ያልኖሩ ሰዎች በሐሳባቸው የፈጠሩት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ያገባኛል ማለት አለበት፡፡ አንዳንዱ ውጭ ይኖራል፣ ይሄዳል፡፡ በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያን የሚያከብሩ አሉ፣ ይወዳሉ፡፡ እዚህም መጥተው  እየሠሩ ያሉ አሉ፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ተወካዮች ይምከሩ፡፡ ይህ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ራዕይና ተልዕኮ ይቀመጣል፡፡ ይህንን ዶ/ር ዓብይ ያስፈጽማሉ፡፡ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል፡፡ ፖለቲካችን በግልብ ሰዎች ከተመራ አደጋ አለው፡፡ ስለዚህ ለጉዳዩ ባለቤት ይሰጠው፡፡ አሁንም የምለው በየአካባቢው ሕዝቡን የሚወክሉ ሰዎች እንዲመክሩ ይደረግ፡፡

%d bloggers like this: