Sat. Oct 24th, 2020

ከወጪ ንግድ ከ2 መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

በሐምሌ ወር ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ እና ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ 252 ነጥብ 19 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 252 ነጥብ 23 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ ይህ ከመቶኛ 100 ነጥብ 02 በመቶ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ አመላክቷል።

አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተገኘው 211 ነጥብ 54 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ40 ነጥብ 69 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር  ወይም 19 ነጥብ 23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።


በበጀት ዓመቱ ሐምሌ ወር ከተያዘው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት የወጪ ምርቶች አበባ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኤሌክትሪክ፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ አትክልት፣ ጫት፣ የብዕርና አገዳ እህሎች እና ቡና ናቸው።

የዕቅዱን ከ75 በመቶ እስከ 99 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች የቁም እንስሳት፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን እንዲሁም ስጋ ናቸው፡፡

ከተያዘላቸው ዕቅድ 50 በመቶ እስከ 74 በመቶ ክንውን ያሰመዘገቡ ምርቶች የቅባት እህሎች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና ቅመማ ቅመም መሆናቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

%d bloggers like this: