Sat. Oct 24th, 2020

በዓሉ ከድንገተኛ አደጋ እና ወንጅል ነፃ መሆኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ ዓመት በዓል የድንገተኛ አደጋና ከወንጀል ድርጊቶች ነጻ በሆነ መልኩ በሰላማዊ መንገድ መከበሩን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታው እንደገለጹት፥ የአዲስ ዓመት በዓል ከዋዜማው ጀምሮ እጅጉን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሯል።


ይህ ዜና እስከተዘገበበት ድረስ “በትራፊክ አደጋ ሰው አልሞተም፤ ከባድ የአካል ጉዳት አልደረሰም፤ ከጸጥታና ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘም ምንም የተከሰሰተ ነገር የለም” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ከህብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ ተግባር በማከናወናቸው በዓሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከበሩን ጠቁመው፥ለዚህም ቀደም ብሎ ከመዲናው ነዋሪ ጋር ተወያይቶ ወደ ስራ በመግባቱ ውጤታማ እንዳደረገ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በዓሉ በሰላም አንዲከበር ከፖሊስ ጎን በመቆም ላደረገው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ ዓመት በዓል ከመድረሱ በፊት ወንጀልን ለመከላከል በተደረገ ዘመቻ ሀሰተኛ የብር ኖቶች፣ የውጭ አገር ገንዘቦች፣ የሀሺሽ እቃዎች፣ ሀሰተኛ ፓስፖርቶች፣ ህገ ወጥ መታወቂያዎች መያዛቸውንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ ዓመት በዓል ምንም አይነት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አለመከሰቱን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የኮምዩኒኬሽ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ከበዓሉ በፊት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በተለያዩ መንገዶች መልዕክቶችን የማስተላለፍ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ።በዚህም የአዲስ ዓመት በዓል ከአደጋ ነጻ ሆኖ መከበሩን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላሳየው ትብብርም ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

%d bloggers like this: