Sat. Oct 24th, 2020

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እየተሰራ ነው

ስቴት ግሪድ የተባለ የሀገረ ቻይና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አምራች ኩባንያ ከአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የስራ ሀላፊዎች ጋር በኤሌትሪክ ኅይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገራችን ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

የስቴት ግሪድ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ሚስተር ቺን ቻኦ ስለ ኩባንያው ስራዎችና የምርት ስርጭት ሽፋን፣ አሰራርና ጠቀሜታው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሊኖር ስለሚችለው ገበያና ጠቀሜታ መግለጻቸውን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘግቧል፡፡


ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2011 ለአለም ባስተዋወቀችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስልቷ የአየር ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ ግብ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መቀነስ ነው፡፡ በዚሁ ማዕቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዞች ከሚቀንሱ ሴክተሮች አንዱ የትራንስፖርት ዘርፍ ሲሆን ይህ ዘርፍ በዋነኛነት ከመኪኖች የሚወጣን ጭስ የሚመለከት ነው፡፡

ይህንን የአየር ብክለት ለማስቀረት ከተቀየሱ አማራጮች አንዱ አረንጓዴ ቴክኖሎጂን መጠቀም ሲሆን በኤሌትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ቀዳሚ ተመራጮች ናቸው ተብሏል፡፡

በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች በስራ ላይ እንዳሉ ተነስቶ ከነዚህም ውስጥ 80%ቱ በአዲስ አበባ እንደሚገኙና የአየር ብክለት ደረጃው ከጊዜ ጊዜ እየባሰ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

አሁን በስራ ላይ ካሉ ተሽከርካሪዎች 15በመቶ የሚሆኑት ብቻ በኤሌትሪክ የሚሰሩ ሲሆን በ2030 ሙሉ በሙሉ በኤሌትሪክ ተሽከርካሪ የመተካት ግብ አስቀምጠው እየሰሩ ስለመሆኑ በውይይቱ ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን የትራንስፖርት አማራጭ በብዙ ምክንያቶች እንደምትፈልገው የገለፁት የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ታዳሽ ሀይልን መሠረት የሚያደርገው የአረንጓዴ ልማት ስልት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እና የተፈጥሮ ጋዝ ጥገኝነትን በማስቀረት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ጉዳዩን ወደስራ ለማስገባት ኮሚሽኑ ተጠሪዎችን የሰየመ ሲሆን የሚመለከታቸውን ሴክተር መ/ቤቶች ያካተተ ምክክር ተካሂዶ የውሳኔ ሀሳብ እንዲቀርብ መጠየቁን የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡

%d bloggers like this: